ሰለ እኛ

This post is also available in: English

”ማስረጃ”  የፍትህ ማእከል

ስለ ማስጃ የፍትህ ማእከል ተልዕኮ ለመስማት እዚህ ይጫኑ [sc_embed_player fileurl=”http://www.masreja.com/wp-content/uploads/2014/09/Masrejja_Audio_Final.mp3″]

ላለፉት 23 አመታት የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ አገዛዝ በአማራ ፣ በኦሮሞ፣ በአፋር፣ በኦጋዴን፣ በሶማሌ ሕዝቦች፣ በጋምቤላ አኙዋኮችና መዠንግር ማህበረሰቦች፣ እንዲሁም በደቡባዊ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ላይ የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ወንጀሎች ፈጽሟል። በልዩ ልዩ ጊዜያት ጥያቄ ያነሱ በርካታ  ኢትዮጵያውያን ለጅምላ ግድያ፣ ሰቆቃ፣ እንግልትና እስር ተዳርገዋል።

በአትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ፣ በክርስትያን ምዕመናን፣ በፖለቲካ  ድርጅቶች አመራሮችና አባላት፣ በጋዜጠኛች፣ በህዝባዊ ድርጅቶች መሪዎችና አባላት፣ እንዲሁም እዚህ ላይ ባልተጠቀሱ በልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የጅምላ ግድያ፣  ሰቆቃና ሌሎች መጠነ ሰፊ ወንጀሎች በሕወሓት አገዛዝ ተፈጽመዋል።

በኢትዮጵያ የሕወሓት አገዛዝ ሰቆቃ ከሚፈፅምባቸው መንገዶች ውስጥ  በተደጋጋሚ በኤሌክትሪክ ሽቦ፣ በሰደፍ፣ በብረት ዱላ፣ ወይም በደረቅ መሣሪያ መደብደብ ፣ጭንቅላትን ውሃ ውስጥ መድፈቅ፣ ዘቅዝቆ በመስቀል መግረፍ፣ የውስጥ ሱሪን አስወልቆ በብልት ላይ ውሃ የሞላ ጠርሙስ አስሮ ማንጠልጠልና ብልት እስኪሟሽሽ ድረስ መቀጥቀጥ፣ በጠጠር ላይ በእንብርክክ ለረዢም ሰዓታት ማስኬድ ፣ ዓይን ተሸፍኖና እጅ በካቴና ታስሮ መደብደብና ግድግዳ ላይ መስቀል፣ የውስጥ እግርን መግረፍ፣ የጣት ጥፍርን ነቅሎ ቁስሉን መርገጥ፣ ጆሮን በጥፊ መምታት፤ አንዱ ከፊት ሌላው ከኋላ ሆኖ ጀርባን፣ ታፋን፣ መቀመጫን፣ ወገብና ትከሻን መደብደብ ። ግድግዳ አስደግፎ ውሃ እያፈሰሱ መደብደብና ማሰቃየት፤ ሰውነት እስኪዝለፈለፍ ስፖርት ማስራትና አቅቶት ሲወድቅ መርገጥ፤ እራስን መቀጥቀጥ፤ የሴቶችን ጡት በኤለትሪክ ገመድ መግረፍ፤ ለረጅም ሰዓት ዘቅዝቆ መስቀል፣ ሲጮህ አፍን በጨርቅ መጠቅጠቅና፤ የተለያዪ ክብረነክ ስድቦችን መስደብ ፣ እጅና እግርን በብረት በማሰር ለብዙ ጊዜ በጨለማ ቤት ለብቻ ማስቀመጥ፤ሰውነትን በኤሌክትሪክ ሃይል መጥበስ ፤ ለረዥም ቀናት ምግብና ውሃ መከልከል፤  ለቀናት እንቅልፍ መከልከል፤  በአንድ እግር ለረጅም ሰዓታት ማስቆም::

ከላይ በጥቂቱ በተጠቀሱት የወያኔ አረመኔያዊ ድርጊቶች ምክንያት ህወሃት ስልጣኑን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ብዙዎች የአካልና የአእምሮ ጉዳተኞች ሆነዋል ብዙዎችም መተኪያ የሌላትን አንድያ ነብሳቸውን ተነጥቀዋል::
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የሀገር ውስጥና ዓለም ዐቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት የወንጀለኛ መቅጫና ሌሎች ሕጎች ያሏት ቢሆንም ቅሉ፤ የሚተገበሩት ግን ከስንት አንድ ጊዜ ነው። አብዛኛዎቹ የሰቆቃ ወንጀሎች በወቅቱና በፍትሐዊነት ምርመራ አልተደረገባቸውም፤ እስከዛሬም ማንም ተጠያቂም አልሆነም።
ስለሆነም እነዚህን ዘግናኝ ወንጀሎች የሚፈጽሙ አካላትን ለማጋለጥና በህግ ፊት ለማቅረብ “ማስረጃ” የፍትህ ማዕከል ትቋቁሟል።

የማዕከሉ ተልዕኮ

 1. ወንጀሎችን ያቀዱ፣ ለወንጀሎቹ ውሳኔ የሰጡ፣ ወሳኔዎችን ያስፈጸሙ፣ የመሩና ያቀነባበሩ፣ እንዲሁም ወንጀሎቹን ፈጽሚዎችን  እራሳቸውን  በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በየትኛውም የምእራብ ሀገሮች እንደየሀገሮቹ የህግ አግባብ መሰረት ክስ ለመመሥረት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ መረጃዎችንና ምስክሮችን ማሰባሰብ እና ማጠናቀር ነው።
 2. ወንጀል በፈጸሙት ላይ በቂ መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ከፍርድ ፊት በማቅረብ በእነዚህ ምዕራብ አገሮች መሸሸጊያ እንዲሁም የመኖሪያ ፈቃድ እንዳያገኙ እንዲሁም ያሸሹት ገንዘብ ሆነ የገዙት ንብረት ካለ ለማሳገድ ነው።
 3. በድህረ ወያኔ፤ በኢትዮጵያ በልዩ አቃቤ ህግ አማካኝነት የወንጀል ክሶች ለመመሥረት የሚያስችሉ መረጃዎች፣ ማስረጃዎች  እንዲሁም ምስክሮች ከወዲሁ ማሰባሰብ፣ ማጠናቀር  እና ዝግጅት ማድረግ ናቸው።

ማዕከሉ የሚያተኩርባቸው  የወንጀል አይነቶች

 1. የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የጦር ወንጀል፣ የጅምላ ግድያዎች፤ አስገድዶ መድፈር ፣ አሰቃቂ ድብደባና ሰቆቃ ::
 2. ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮችና አባላትን፤  የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን እንዲሁም ንጹሐን ዜጎችን ያለ ሕግ አግባብ ማሰር፣ አፈና በማድረግ ሰቆቃ መፈጸም ::
 3. በጎረቤት ሀገሮች ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ እንዲሁም ዩጋንዳ እና የመን  የሕወሓት የደህንነት ሹሞችና ሰላዮች ዜጎችን መጥለፍና ደብዛ ማጥፋት::
 4. ዜጎችን ከቤት ንብረት ማፈናቀል፣ በተማና በገጠር መሬትን መንጠቅና አገር  በቀል የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን የቀረጥ ተመንን በመጫን እንዲዘጉ ማድረግ፣ በከተማ ልማት ሽፋን በአነስተኛ የካሳ ክፍያ በርካታ ዜጐችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀልና በከፍተኛ  ገንዘብ ለባለሃብቶች መሸጥን ያጠቃልላል።

ማስረጃ የሚሰባሰብባቸው ተፈላጊዎች ዝርዝር በቅደም ተከተል

 1. የሕወሓትና የአሕአዴግ የሲቪል ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ውሳኔ ሰጭዎች፣
 2. የሕወሓት/ኢሕአዴግ  የደህንነት፣ ወታደራዊና የፌዴራል ፓሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ አዛዦችና ውሳኔ ሰጭዎች፣
 3. በየእርከኑ የሚገኙ የሕወሓት/ኢሕአዴግ የመከላከያ አዛዦች፣ የደህንነት የፌዲራል ፓሊስ ውሳኔ አስፈጽሚዎች፣ ውሳኔ ፈጻሚዎች ፣ ሰቆቃ ፈጻሚና ገራፊ መርማሪዎች፣
 4. በዜጎች ላይ በግፍ የፈረዱ፣ ከወንጀለኞች የተባበሩና በየእርከኑ የሚገኙ የፌደራልና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችና አቃብያነ  ህግ፣
 5. በየክልሉ በየደረጃው  የሚገኙ የፌደራልና  የክልል ፖሊስ አዛዦች፣ የልዩ ሃይል አዛዦች፣  የፖሊስ መሪማሪዎች፣  በየክልሉ የሚገኙ የደህንነት ሃላፊዎች፣ ቁልፍ የደህንነት አባላት፣ የየክልሉ ሚሊሽያ አዛዦችና በተዋረድ የሚገኙ ሹሞች፣
 6. በየእርከኑ የሚገኙና በግፍ በዜጎች  ላይ ፍርድ በመስጠት ንጹሃን ዜጎችን ያጠቁና ያስጠቁ ዳኞችና አቃብያነ  ህግ፣
 7. በተለያዩ የሃገሪቱ የአስተዳደር ክልሎች ከየማዘጋጃ ቤቱ ህጋዊ የቤት ባለቤትነት ይዞታና የካርታ ማስረጃዎችን አሰርቀው በማውጣት የተጭበረበረ ሰነዶችን እያቀረቡ የህዝብን ንብረት የወሰዱና ለዚህም ተግባራቸው የተባበሯቸውን ግለስቦች ማንነት፣
 8. በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከህጋዊ ጨረታ ውጪ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር በመመሳጠር በኰሚሽንና በሃሰት በተዘጋጀ የሰነድ ማስረጃ በርካታ ገንዘብ የዘረፉ ግለሰቦች ማንነትና ዝርዝር የወንጀል ድርጊቶች፣
 9. ከአገር ወደ ውጪ፣ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡና እንዲወጡ በማድረግ በአየር ለአየር ንግድ የከበሩና ህጋዊ የንግድ ድርጅቶችን በማዘጋት የግል ሃብትና ንብረት እየዘረፉ የሚገኙ ሰዎችን ማንነትና አድራጐት በዝርዝር፣
 10. “የትግራይ ባለሃብቶችን” ለመፍጠር በሚል ስሌት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በመንግስት ይዞታ ስር  የነበሩ ለም መሬቶችን፣ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን እጅግ በጣም አነስተኛ በሆነ ክፍያ በአብዛኛውም በልዩ ትዕዛዝ የተቸራቸው ግለሰቦች ዝርዝርና ፤ ይህንንም ያስፈፀሙ የወንጀል ተባባሪዎችን ማንነት::

በኢትዮጵያ ውስጥ ቤተሰብ ዘመድ በአገዛዙ የተገደሉባችሁ ፣ አሰቃቂ ድብደባ ፣ ሰቆቃ የተፈጸመባችሁ ፤ በየጊዜው ስለተፈፀሙ ልዩ ልዩ መንግስታዊ ወንጀሎች፣ ግፍ፣ ግድያ፣ ሰቆቃ፣ አድራጊዎች/ፈጻሚዎች ማንነት የምታውቁ፣ ቤተስብ፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ የደረሱበትን የማታውቁ፣ ወንጀሎች የት፣ በማን፣ መቼ እንደተፈጸሙ የምታውቁ፣ እማኝ የሆናችሁ፣ ወንጀሎችን በሚመለክት ያዩ፣ የሰሙ ግለሰቦችን የምታውቁ፤ ስለወንጀሎቹ ዝርዝርና ሰለአድራጊዎቹ ማንነት የምታውቁ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የሚያካትቱ መረጃዎችን ለማዕከሉ በመስጠት እንድትተባበሩ ጥሪ እናደርጋለን።

 1. በወንጀል ተፈላጊ ሹማምንት  ሙሉ ስም፣
 2. ወንጀሉን በሚመለክት በእጅ የሚገኙ/የሚታወቁ ዝርዝር መረጃዎች (መቼ፣ የት፣ በምን      ምክነያት፣ በማን)፣
 3. በወንጀል ተፈላጊ  የቅርብ ጊዜ ፎቶዎች፣
 4. በወንጀል ተፈላጊ ግለሰቦች የስራ አድራሻ፣ የስራ ባልደረቦችና ከስራ ቦታዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎች፣
 5. በወንጀል ተፈላጊ  ግለሰቦች የመኖሪያ አድራሻ፣ የቤተሰብ ሁኔታ ዝርዝር መረጃዎች፣
 6. በወንጀል ተፈላጊ ግለስቦች በማህበራዊ ቦታዎችና በመዝናኛ ቦታዎች ሁሉ የተነሱ ፎቶግራፎች ቪዲዮዎች (በሞባይልና በሌላ መሣሪያ የተቀረጹ መረጃዎች)፣
 7. በወንጀል ተፈላጊ ግለሰቦች ከቦታ ቦታ እንቃስቃሴና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጉዞ ሁኔታ መረጃዎች፣
 8. በወንጀል ተፈላጊ ግለሰቦች  የንብረት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር የተያያዙ መረጃዎችና ሰነዶች፣
 9. በወንጀል ተፈላጊ ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች የሀገር ሃብትና ንብረት ከመዝረፍና ያለአግባብ ሃብት ከማፍራት ጋር የተያያዙ መረጃዎችና ሰነዶች፣

በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተፈጸሙና  ሰለሚፈጸሙ የመንግስታዊ ሽብር ፤  የሰበዓዊ መብቶች ረገጣ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፤  ሰባዓዊ መበቶችን የሚረግጡ  ወንጀለኞች  ጋር የተያያዙ ያገኙትንና የሚያውቁትን ማንኛውንም መረጃዎች፤ የማሰረጃ ሰነዶችን፤ ፎቶዎችን  ለመስጠት/ለመላክ  በሚከተለው የማስረጃ የመልዕክት መስጫ አገልግሎት ስልክ ይደውሉ።

ለማስረጃ ስልክ መልእክት ለመስማት እዚህ ይጫኑ  [sc_embed_player fileurl=”http://www.masreja.com/wp-content/uploads/2014/11/masreja_message_center_audio.mp3″]

ስልክ ቁጥር ፡ 1 (800) 385-1804
መረጃዎች፤ የማሰረጃ ሰነዶችን፤ በኢሜል ለመላክ ለምትፈልጉ editor@masreja.com ይላኩልን
ለማስረጃ ስልክ መልእክት ለመስማት እዚህ ይጫኑ 

በመንግስታዊ ኃላፊነት  ላይ የነበሩና አሁንም የሚገኙ የሰበአዊ መብት ረጋጮችን  በሚመልከት ማንኛውንም አይነት መረጃና ማስረጃዎችን  በማስተላለፍ   ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ የድርሻቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን!!፡

”ማስረጃ”  የፍትህ ማእከል
==========================================================

የዓለም ዐቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትርጓሜዎች

ዘር ማጥፋት

በሮማው ሕግ መሠረት “ዘር ማጥፋት”ማለት አንድን ብሔር ወይም ጎሳ ወይም ሃይማኖታዊ ስብስብ፤ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የሚከተሉትን ተግባራት መፈፀም ነው፡-

 • ግድያ
 • የጅምላ ግድያ
 • በባርነት ማሳደር
 • ሕዝብን ከቀዬ ማፈናቀል ወይም በግዳጅ ማስፈር
 • ማሰር
 • ሰቆቃ መፈፀም
 • አስገድዶ መድፈር፣ በወሲብ ባርነት ማሳደር፣ በግዳጅ ለወሲብ ሸቀጥነት ማሰማራት፣ አስገድዶ ማስፀነስ፣ አስገድዶ ማምከን፣ ወይም የትኛውም አይነት ከፍተኛ የሆነ ወሲባዊ ጥቃት መፈፀም
 • አንድን የተለየ ስብስብ በፖለቲካ፣ በዘር፣ በብሔር፣ በጎሳ፣ በባሕል፣ በፆታ አማካኝነት ማዋከብና ማሰቃየት
 • የግለሰቦችን ደብዛ ማጥፋት
 • “የአፓርታይድ” (በዘር በመለየት) ወንጀል መፈፀም
 • ሌሎች ተመሳሳይ ሆን ተብሎ ከፍተኛ ሰቆቃ፣ የአካል እንዲሁም የአዕምሮ ጉዳት ለማድረስ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ እርምጃዎችን መፈፀም

የጦር ወንጀል

የጦር ወንጀል የሚያጠቃልላቸው፤ መጠነ ሰፊ የሆኑ የጄኔቫ ስምምነት ጥሰቶች፣ እንዲሁም በዓለም ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ይዘት በሌላቸው የትጥቅ ግጭቶች ላይ የፀኑና በሮማው ሕግ ላይ የሰፈሩ ዓለም ዐቀፍ ሕግጋትና ደንቦች ጥሰቶች ሲሆን እነዚህ መጠነ ሰፊ የዓለም ዐቀፍ ሕግጋት ጥሰቶች የተፈፀሙት በዕቅድ፣ በፖሊሲ ወይንም በከፍተኛ መጠን ሲሆን ነው። እነዚህ የተከለከሉ ተግባራትም እንደሚከተለው ይሆናሉ፡-

 • ግድያ፣
 • ወሲባዊ ጥቃት፣ የጭካኔ አያያዝ፣ ሰቆቃ መፈፀም፣
 • ጠልፎ በመያዣነት መጠቀም፣
 • በሕዝብ ላይ ሆን ብሎ ጥቃት መፈፀም፣
 • ለኃይማኖት፣ ትምህርት፣ ሥነ-ጥበብ፣ ሥነ-ሕይወት (ሳይንስ)፣ በጎ አድራጎት፣ የሕክምና ማዕከል የተቋቋሙ ሕንፃዎች ላይ እንዲሁም በታሪካዊ ሃውልቶች ላይ ሆን ብሎ ጥቃት መፈፀም፣
 • የኃይል (የትጥቅ) ዝርፊያ፣
 • አስገድዶ መድፈር፣ በወሲብ ባርነት ማሳደር፣ በግዳጅ ማስፀነስ፣ ወይም የትኛውም አይነት ከፍተኛ የሆነ ወሲባዊ ጥቃት መፈፀም፣
 • ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን ለውትድርና ማሰማራት፣ ወይንም ለተመሳሳይ የትጥቅ ቡድን ማሰለፍ፣ ወይንም ሚደረጉ የትጥቅ ጥቃቶች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ መጠቀም።

የጦር ወንጀል ፡ የዘር ማጽዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች  በኢትዮጵያ

በታህሣስ ወር 1996፣ በጋምቤላ – ኢትዮጵያ፣ ባንድ ቀን 424 ሰዎች የሕወሓት ታማኝ በሆኑ የደህንነት ኃይሎች ከሕግ አግባብ ውጪ ተገድለዋል። በኢትዮጵያ በስፋት እየተካሄደ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የጦር ወንጀልን በተመለከተ ማስረጃው በሚገባ የተጠናቀረና ከፍተኛ አግራሞትን የሚፈጥር ነው። በኢትዮጵያ፤ በ1997 ዓ.ም. ለተደረገው ምርጫ በዕውቅ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን በሕወሓት መራሹ አገዛዝ ላይ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በድኅረ-ምርጫ ወቅት በተቀሰቀሰው ሰላማዊ ተቃውሞ 193 ሰዎች ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ በአገዛዙ የደህንነትና ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ፌዴራል ፖሊሶች ተገድለዋል፣ 763 ሰዎች ቆስለዋል፣ ሌሎች 30,000 ሰዎች ደግሞ ያለምንም ክስ ከከተማ ውጪ በሚገኙ ማጎሪያ ካምፖች ታስረዋል። በእነዚህ ወንጀሎች ቢያንስ 237 ግለሰቦች በመፈፀምና በማስፈፀም ተለይተው ታውቀዋል።
በ2008 ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ በኦጋዴን የተፈፀመውን የ150 ሰዎች እንዲሁም ሌሎች 37 ሰዎች የብቀላ መረሸን ኃላፊነቱን ለኢትዮጵያው አገዛዝ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡- “ባልታጠቁ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ያዘዘው ወይንም በመፈፀም የተሳተፈው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል በጦር ወንጀለኛነት ተጠያቂ መሆን አለበት። ስለእነዚህ ወንጀሎች ዕውቀት ያላቸው ወይንም ማወቅ የነበረባቸውና (ጥቃቱን ለማስቆም) ምንም አይነት እርምጃ ያልወሰዱ ከፍተኛ የጦር እንዲሁም የሲቪል መኮንኖች፤ በአመራር ዕዝ ምክንያት ባላቸው ኃላፊነት በወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ። መጠነ ሰፊ የሆኑና ስልታዊ ባህሪ ያላቸው በሶማሌ መንደሮች ላይ የተደረጉት ጥቃቶች፤ ግድያው፣ ሰቆቃ መፈፀሙ፣ አስገድዶ መድፈሩ፣ እንዲሁም ማፈናቀሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነት ለመሆኑ አሌ የማይባል ማስረጃዎች ናቸው።”

የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት፣ እና ሰቆቃ  በሕወሓት ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ የሚደረገው የሀገር ክህደት እና ሽብርተኝነት ክስ የሚደረገው በይስሙላ ፍርድ ቤት ነው። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ባወጣው የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት መሠረት፤ “የኢትዮጵያ “ፀረ-ሽብር ሕግ” ፖለቲካዊ አላማ ያለውና የተቃዋሚ አመራሮችን፣ ዴሞክራሲ አራማጆችን፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችን፣ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን ለመክሰስ እና ለማሰር እንዲሁም የመገኛኛ ብዙሃን የሕትመት ሥራዎችን ለማጥፋት ታቅዶና ታልሞ የወጣ ሕግ ነው” ብሎ አስቀምጦታል። የመንግሥት ሚና ከሕግ አስፈፃሚው ባልተለየበትና ዳኞች ውሳኔ ከመንግሥት በትዕዛዝ በሚቀበሉበት ሀገር፤ ማንኛውም ክስ፣ የፍርድ ውሳኔ እንዲሁም የሞት ቅጣት የሕግ አግባብነት ያለው አይሆንም።
ሂዩማን ራይትስ ዎች “ሕጉ የሽብርተኝነትን ትርጓሜ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ያለው እና አሻሚ አድርጎ ያስቀመጠው ሲሆን፤ በሽብርተኝነት መፈረጅ የሌለባቸውን ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ተቃውሞንና ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን እንደሽብር ወንጀል ለመቁጠር ያገለግላል” ብሎ ገልፆታል። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ተቃውሞውን “እጅግ በጣም የከፋ እና ፖለቲካዊ ዓለማ ባዘለ መልኩ ተቃዋሚዎችን በጥፋተኛነት ለመክሰስ ሥራ ላይ የዋለ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ሕግ” በማለት አትቷል።

የፀረ-ሰቆቃ ስምምነት

በመንግሥት ትዕዛዝ ከሚፈፀም ሰቆቃ ነፃ የመሆን መብት፤ በዓለም ዐቀፍ ሕግና ከፍተኛ መርሆች ዕውቅና ያለው መሠረታዊ ዓለም ዐቀፍ መብት ነው። ኢትዮጵያ የፀረ-ሰቆቃ ስምምነትና የሌሎች የከፉ፣ ኢ-ሰብአዊ ወይንም የዘቀጡ አያያዞች ወይንም ቅጣቶችን ስምምነት መጋቢት 5 ቀን 1986 ዓ.ም. ፈርማለች። የዚሁ ስምምነት አንቀጽ 1 ሰቆቃን “በሰው አዕምሮ ወይንም አካል ላይ ከፍተኛ ሕመም እና ሥቃይ ሆን ብሎ በማድረስ፤ መረጃን ከግለሰብ ወይንም ከሦስተኛ ሰው ለማግኘት ወይንም ለማናዘዝ የሚደረግ ማናቸውም ተግባር … [ብሎም] … ይህ ሕመምና ሥቃይ በመንግሥት ኃላፊ ወይንም ሌላ በመንግሥት የኃላፊነት ቦታ ላይ እራሱን አስቀምጦ በሚሠራ ሰው አማካኝነት፣ ወይንም ጠንሳሽነት፣ ወይንም ዕውቀት፣ ወይንም ተቀባይነት የተፈፀመ ተግባር።” በማለት ትርጉሙን ያስቀምጣል።
ሰቆቃ እና መብት ረገጣ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ የደህንነት ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙትን ሰቆቃና መብት ረገጣዎች መዝግበው አስቀምጠዋል። “የኢትዮጵያ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና የደህንነት ኃይሎች፤ አምባገነናዊ አገዛዙን ይቃወማሉ ያላቸውን መጠነ-ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍል፣ ማለትም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ መንግሥት አማጽያን እና ሽብርተኛ ብሎ የፈረጃቸውን ቡድኖች ይደግፋሉ ብለው የሚጠረጥሯቸውን ዜጎች ላይ ቅጣት ያደርሳሉ። በማዕከላዊና ክልላዊ መንግሥታት ተወካዮች የሚፈፀመው ግፍ መጠንና ድግግሞሽ እንዲሁም በሁሉም ቦታ ላይ በተመሳሳይ መልኩ የመንሰራፋቱ ፀባይ ወይም ባህሪ፤ ጋጠወጥ በሆኑ ወታደሮች ወይም ፖሊሶች የሚፈፀም ተግባር ሳይሆን፤ የከፍተኛ ባለማዕረግ አዛዦች ያሉበት በስልታዊነት የሚፈፀም የግፍ ተግባር መሆኑን ያሳያል። ሂዩማን ራይትስ ዎች በማስረጃ ባጠናቀራቸው በርካታ ክስተቶች ላይም ወታደራዊ አዛዦች በግል ሰቆቃ ፈፅመዋል።

Masreja Advert

Tamagne Beyene's Interview with ESAT About Masreja